ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሁከት፣ ብጥብጥ እና የንግድ ቤቶች ዘርፋ ተይዘው የነበሩ 600 እስረኞች በዋና ከተማዋ ጁባ ከሚገኝ ወታደራዊ እስር ቤት አምልጠዋል ሲል የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
የሀገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጆን ካሳራ ኮአንግ ኒያል ጉዳዩን አስመልከተው በሰጡት መግለጫ፤ ፖሊስ ጥይት ወደ ላይ በመተኮስ፤ ካመለጡት መካከል 410 የሚደርሱ ወንጀለኞችን ዳግም መያዙን ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ የቀሩትን ያመለጡ እስረኞች በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝም ቃል አቀባዩ መናገራቸውን አናዶሎ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት በሱዳን በአልጃዚራ ግዛት ዋና ከተማ ዋድ ማዳኒ የተገደሉትን ከ20 በላይ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ዜጎች የሚያሳዩ አሰቃቂ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጩ በኋላ በሀገሪቱ ከባድ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ብዙ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በጦርነት በምትታመሰው ጎረቤት ሱዳን ታግተው እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፤ ቪዲዮዎቹ በአገራቸው የሚኖሩ የሱዳን ዜጎችን በማጥቃት አጸፋዊ ምላሽ እንዲሰጡ በተቃውሞ ሰልፍ ጠይቀዋል።
ፖሊስ ሰኞ ዕለት እንዳረጋገጠው በተቃውሞ ሰልፉ 16 የሱዳን ዜጎች ሲገደሉ፣ በርካታ የንግድ ቤታቸው ወድሟል ወይም ተዘርፏል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በደቡብ ሱዳን ሲቪሎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እንዲያቆም ያሳሰቡ ሲሆን፤ ሕዝቡም ከበቀል እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
ይህ ደግሞ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ውጥረት ሊያስሳ ይችላል የሚሉም ስጋቶች በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ ነው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በደቡብ ሱዳን 600 እስረኞች ማምለጣቸው ተሰማ
ካመለጡት መካከል 410 የሚደርሱ ዳግም መያዛቸው ተገልጿል
