ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከመስመር ውጪ ለአሽከርካሪዎች በማይታይ መልኩ ተደብቀው ክትትል የሚያደርጉ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሥራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል።
"ይህንን ሥራ የሚሰሩ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ትክክል ናቸው፣ አጠናክረን ነው የምንቀጥለው፣ ተደብቀው ቁጥጥር እንዲያደርጉም እንመክራለን፤ ምክንያቱም አሽከርካሪ ሁልጊዜም ሕግን እንጂ ተቆጣጣሪን አክብሮ መንቀሳቀስ የለበትም" ሲሉ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ ለአሐዱ ገልጸዋል።
"ተቆጣጣሪዎች ሲኖሩ ሕግ የሚከበርበት፤ ሳይኖሩ ደግሞ እንደተፈለገ ሕግ የሚጣስበት ሁኔታ መኖር የለበትም" በማለትም አክለዋል።
በዚህም "በአሽከርካሪዎች ዘንድ 'የሚከታተል አካል ከሌለ ጥፋት እናጠፋለን' የሚል ልምምድ እንዳይኖር ተቆጣጣሪዎች በግልፅ በመታየትም ሆነ በስውር ቁጥጥር እንዲያደርጉ እናበረታታለን" ብለዋል።
"ይህ የሚደረገውም አሽከርካሪው 'ተቆጣጣሪዎች አሉ?' ወይስ 'የሉም' የሚል ፍለጋ ውስጥ እንዲገባ ሳይሆን፤ ሕግና ስርዓትን በማክበር ብቻ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ በመሆኑ ነው" ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም በግልፅና በድብቅ የሚሰራው ሥራ የትራፊክ ቁጥጥር ከሚደረግበት መንገድ ውስጥ አንዱ እና አደጋዎችንም ለመቀነስ ታስቦ ስለሆነ አሽከርካሪው በደንብ መገንዘብ እንደሚገባው አስታውቀዋል።
"በሌሎች የዓለማችን ሀገራት ላይ በምናየው ተሞክሮ የትኛውም አሽከርካሪ 'ተቆጣጣሪ አለ' ወይስ 'የለም' የሚለውን ሳይሆን፤ በየትኛውም ቦታ ቢሆን በሚቀረፅ ተንቀሳቃሽ ምስል መታየቱ ስለማይቀር ሕግ ማክበሩን ብቻ እንደሚያይ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በመዲናዋም አሁን ላይ እየተሰራበት የሚገኘው በቴክኖሎጂ የመቆጣጠር ዘዴ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ሲገባ እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስከዚያው ግን በድብቅና በግልፅ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስታወስ፤ አሽከርካሪዎችም ሕግና ስርዓት ማክበራቸውን እንጂ ተቆጣጣሪዎችን ብቻ ማየት እንደማይገባቸው አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ