ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች ፎረም "ብሔራዊ መግባባት" በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ በትናትናው ዕለት ተካሂዷል።
በውይይቱም "ሀገር አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ችግሮች ሳይፈቱ የፖለቲካ መግባባትና ሀገራዊ ምክክር ማድረግ እንዴት ይቻላል?" ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጠይቀዋል።
"ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት 'የፖለቲካ ቅርቃር ለመውጣት' የብሔራዊ መግባባትና ምክክር የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ ባለው ተክታታይ የፖለቲካ ቀውስ፣ ግጭት እና የእርስ በእርስ ጦርነት አውድ ውስጥ ምን አይነት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ይቻላል?" ሲሉም ጥያቄያቸውን አቀርበዋል።
አክለውም ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ሃብት፣ የዜጎች ሞት፣ የማህበራዊ ትስስር መበጠስ እና በዜጎች እና በመንግሥት መካከል ያለው መተማመን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል ብለዋል።
"በውይይት መድረኩ የመነሻ ሃሳብ በብሔራዊ መግባባት ላይ የቀረቡት ተግዳሮት ላይም ቢሆን በሀገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ወደ መጨረሻ አለመንሳቱን እና በሚፈለገው ልክ ትኩረት አልተሰጠውም" ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ገልጸዋል።
"አሁን ላይ ልናደርጋቸው የሚገቡ ማሻሻያዎች መመልከት አለብን" ያሉም ሲሆን፤ "በመንግሥትና በታጣቂዎች መካከል ያለውን ግጭት ማስቆም የግድ ይላል" ብለዋል።
'የወል ትርክት የጋራ መዳረሻ ራዕይ ያለው መሪ መኖር አስፈላጊ ነው' በሚል የተቀመጠው የምፍትሔ ሃሳብ በጎ ቢሆንም አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን ይህን አይነት መሪ ስለመኖሩ ጠይቀዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን በሁሉም አካባቢዎች ያለውን ውጊያ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ