መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በቦሌ ክፍለ ከተማ ፒኮክ መናፈሻ አካባቢ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የነበሩ 13 ሰዎች በጎርፍ ተከበው መውጫ እንዲያጡ ምክንያት ሆኖ እንደነበር የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ጥቆማው እንደደረሳቸው በፍጥነት በመድረስ ባካሄዱት ርብርብ መሰላል፣ ገመድ እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመጠቀም አስራ ሦስቱን ሰዎች በሕይወት ማትረፍ ችለዋል፡፡

አቶ ንጋቱ አክለውም ትላንት ማክሰኞ በመዲናዋ የጣለው ዝናብ በጎርፍ ከተከበቡት ሰዎች በተጨማሪ በተወሰኑ ቤቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰ የገለጹ ሲሆን፤ በደንበል እና ብሔረ ጽጌ አካባቢ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ባሉ ቁሶች ላይ መጠነኛ አደጋ ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የትራፊክ መንገዶች በጎርፉ በመሙላታቸው መስመሮች እንዲጨናነቁ ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና ማህበረሰቡም ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚሰጡ መረጃዎችን በማዳመጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
በበልግ ወቅት አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቅድመ ጥንቃቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት ባለሙያው፤ ኮሚሽኑ ለሚደርሱ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አክለውም ባለፈው ዓመት የበልግ ዝናብ የሰዎችን ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰው፤ "በተለይ ወንዝ ዳር አካባቢ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአደጋው ተጋላጭ እንደመሆናቸው ጥንቃቄ ሊደረጉ ይገባል" ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ