መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በአዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀጽ 94 መስረት በግል ሥራ የተሰማሩ ነጋዴና ተቀጣሪ ዜጎች አምሽተው እንዲሰሩ የሚያዝ ደንብ አውጥቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ደምብ 185/2017 የተሰኘ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምሽት 4 ሰዓት ድረስ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ ተቋማት ደግሞ ምሽት 3:30 ድረስ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ደንብ ከመጋቢት 10 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል።

ደንቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ያጸደቀው የካቲት 29/2017 ዓ/ም የነበረ ሲሆን፤ ይህ ደንብ መመሪያዎች ተዘጋጅተውለት ከመጋቢት 10/2017 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

አሐዱም "ይህ ጉዳይ ከመሠረታዊ የሕገ-መንግሥት መሠረታዊ ሁነቶች የሚጣራስ አይደለም ወይ? በተለይም የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ በሚለው አንቀጽ ላይ 'ዜጎች ከፍላጎታቸው ውጭ ተገደው መሰራትን' አስመልክቶ የወጣውን ድንጋጌ አይጥስም ወይ?" ሲል የሕግ ባለሙያዎች ጠይቋል፡፡

ለአሐዱ ሀሳባቸውን የሰጡት የሕግ ባለሙያው ሹመት ጌትነት "ይህ አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ አስፈፃሚ አካላትን ለማቋቋም እንደገና ተሸሽሎ የወጣ አዋጅ ነው" ብለዋል፡፡

"በመሆኑም ይህ አዋጅ የከተማዋን አስፈፃሚ አካላትን የሚመለከት ይሆናል እንጂ፤ ሁሉም የግል ነጋዴ እና ተቀጣሪ ሠራተኞችን የሚያካትት ይሆናል የሚል ግምት የለኝም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አዋጁ በሕጉ መሠረት የሥራ አሰፈፃሚዎችን የሚያስገድድ እንጂ የግል ነጋዴዎችም ሆነ የግል ተቀጣሪዎችን የሚመለከት አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም "የወጣው ደንብ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው" ያሉት የሕግ ባለሙያው፤ "ካቢኔው ይህንን እንዲያስወጣ የተሠጠው ስልጣንም የለም" ብለዋል፡፡

ከዚህም በላይ የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት የሚጥስ መሆኑን በማንሳት፤ "ማንም ሰው ተገዶ በንብረቱ ሊታዘዝ አይገባም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"በአሁን ወቅት እየወጡ ያሉ ሕጎች አብዛኛው አስገዳጅ ናቸው" የሚሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ቶማስ አየለ በበኩላቸው፤ ከቀድሞ ሕጎች ጋር ሲታይ አስተማሪነታቸው የቀነሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡

"ደንቡን ተላልፈው በሚገኙት ላይ እስከ 10 ሺሕ ብር ቅጣት መጣል ተገቢ አይደለም" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ከነጋዴዎች እና ተቀጣሪዎች በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እስከ 4 ሰዓት እንዲሰሩ የሚያስገድደው ደንብ ላይ ቅሬታ እየተነሳበት ይገኛል፡፡

በመሠረቱም የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 3 ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ 'ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት ሲባል ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው' ሲል ይደነግጋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ