ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተያዘው 2017 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ውስጥ ቁጥጥር ከተደረገባቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ አሽከርካሪዎች መካከል፤ 23 ሺሕ 370ዎቹ የተቀመጠውን መመሪያ የጣሱ በመሆናቸው እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ለአሐዱ በላከው መረጃ አስታውቋል።
ቢሮው በ6 ወር ውስጥ ቁጥጥር ለማድረግ ከታቀደው አጠቃላይ 2 ሚሊዮን 981 ሺሕ 384 መካከል፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አሸከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ማድረጉን ገልጿል። እንዲሁም ከታቀደው አንጻር ሲታይ አፈጻፀሙ የቀነሰ መሆኑንም ገልጿል።
ለዚህም ምክንያት በታቀደው ልክ ለመስራት ፈጻሚዎች 'ከአድርባይነት' ወጥተው ሥራዎችን ከመመሪያና ደንቦች አንፃር መተግበር ላይ ጉድለት መኖሩና የወጡ ሕጎችን በፍጥነት ተግባራዊ ባለመደረጉ እንዲሁም፤ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ተግዳሮት እንደሆነበት አንስቷል።
በዋናነት እርምጃው ትርፍ በመጫን፣ ታሪፍ በመጨመር በሦስተኛ ወገን የተቀጣ፣ በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ፣ ቀበቶ ባለማድረግ፣ ያለ መንጃ ፈቃድ በማሽከርከር እንዲሁም የመናኸሪያ መውጫ ሳይዙ ሲሰሩ በተገኙ አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደባቸው መሆኑም ተገልጿል።
የእርምጃ አወሳሰዱን በተመለከተ የብር ቅጣትና ከሥራ ማገድ እንዲሁም የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑንም አስታውቋል።
እንደ አጠቃላይ ያለው የጸጥታ ችግር እንዲሁም መሰል የአሰራር ክፍተቶች ተግዳሮት ቢሆንበትም፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ መረጃው አመላክቷል።
በተጨማሪም ሕገ ወጥነት የሚበዛበትን ቀን፣ ሰዓትና ቦታ በመለየት ለመቆጣጠር ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ጠቁሟል።
ቢሮው አክሎም በየጊዜው የሚፈጠሩ የአሰራር ክፍተቶችን ግልጽ ውይይት በማድረግ በዞንና በከተማ ደረጃ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር ችግሮቹ የሚፈቱ መሆኑን አብራርቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ