ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው ሳውዲ አረቢያ፣ የመን፣ ቤሩት እና የመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 33 ሺህ 9 መቶ የሚጠጉ ስደተኞች ባለፉት 6 ወራት ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከስደት ተመላሾቹ ከሳውዲ አረቢያ 31 ሺሕ 358፣ ከየመን 2 ሺሕ 304፣ ከቤሩት 237 ሰዎች በድምሩ ሕጻናትን ጨምሮ 33 ሺሕ 900 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጄ ተግይበሉ፤ ከተመላሾቹ መካከል 1 ሺሕ 60 የሚሆኑት ከፍተኛ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 2 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሀገር መመለሳቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፤ በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተመለሱት 152 ሺሕ 349 ከስደት ተመላሾች መካከል 47 ሰዎች ከፍተኛ የአካል የሆነ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
አክለውም ተቋማቸው፤ ለችግር የተጋለጡ እና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ከባለድርሻ አካላት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የድጋፍ ሥራዎች እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከስደት ተመላሾቹ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እንደ ‹ዊልቸር› ያሉ ድጋፎችን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ፤ "ምግብ እና መጠለያ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙና ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል፡፡
ዜጎችን ለሕገ-ወጥ ደላሎች አሳልፈው የሚሰጡ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግም እየተሰራ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ