ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዕምሮ ሕመምተኞችን ለመርዳት ጥቅም ላይ የሚውሉ መድኃኒቶች እጥረት በመኖሩ ታካሚዎችን በበቂ ሁኔታ መርዳት እንዳልተቻለ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር አስታውቋል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት እሌኒ ምስጋናው፤ የመድኃኒት እጥረቱ የተከሰተው በአዕምሮ ሕመም የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ በማሻቀቡ እንደሆነ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የመድኃኒት ፍላጎቱን ሀገር ውስጥ በሚመረቱ እና ከውጭ ሀገር በሚገቡ መድኃኒቶች ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ ከታማሚዎች ቁጥር አንጻር በቂ እንዳልሆነ አንስተዋል።

በአማኑዔል የአዕምሮ ስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ሳሙኤል ቶሎሳ በበኩላቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር መጨመር የመድኃኒት እጥረት እያስከተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ከአዳዲስ ታካሚዎች በተጨማሪ ከሌሎች የሕክምና ተቋማት በሪፈር የሚላኩ ታካሚዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚገኝ ነግረውናል።

"ማኅበረሰቡ የአዕምሮ ህመም ያጋጠማቸው ሰዎች በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ ከማድረግ ይልቅ በመንፈሳዊ መንገድ ፈውስ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል"ያሉት ባለሙያዎቹ፤ ታማሚዎች በሽታቸው ሥር ከሰደደ በኋላ የሚሰጣቸው ሕክምና ለውጥ የማስገኘት ዕድሉ ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ችግሩ ያጋጠማቸውን ሰዎች በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ