መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከወራት በፊት በጠለምት ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ100 በላይ አባዎራዎች አሁን ላይ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለአሐዱ አስታውቋል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በድሉ ዘውዴ አሁንም ድረስ 119 የሚደርሱ አባዎራዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በአደጋው ተፈናቅለው አሁን ላይ በተለያዩ የመጠለያ ካምፖች እና ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ በጊዜያዊነት ተጠልለው የሚገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
"ለተፈናቃዮቹ አደጋው በተከሰተ ሰሞን ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ግን አልተቻለም" ያሉት ኃላፊው፤ ከእርዳታ በተጨማሪ የጊዜያዊ መጠለያ እና ዘላቂ የሆነ መኖሪያ ቤት ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
አክለውም አሁን ላይ ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ከግል ባለሃብቶች ይቀርቡ የነበሩ የምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ ድጋፎች መቋረጣቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ተፈናቃዮቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ በመሬት መንሸራተት አደጋው ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው እና የእርሻ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በመውደሙም፤ እነርሱን መልሶ ለማቋቋም እንዲሁም ዘላቂ የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች በሂደት ላይ እንደሚገኙም ኃላፊው አብራርተዋል።
አክለውም ክረምቱ መቃረቡን ተከትሎ ተፈናቃዮቹን ወደ አጎራባች ወረዳዎች ለማዘዋወር ጥረት የሚደረግ መሆኑን አንስተው፤ "ያ መሆን ካልቻለ ግን አንድ ቦታ ላይ ለማስፈር ከክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር ይሰራል" ብለዋል፡፡
"ተፈናቃዮቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም የላቸውም" ሲሉም ጨምረው ለአሐዱ አስታውቀዋል፡፡
በጠለምት ወረዳ አብና ቀበሌ ልዩ ሥሙ ኖላ በተባለ ቦታ ላይ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት፤ 10 ሰዎችን ሕይወታቸው ማለፋ ይታወሳል።
የመሬት መንሸራተት አደጋው የሰዎች ሕይወት ከመቅጠፉ በተጨማሪ 35 የቤት እንሰሳቶች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በአደጋው ከ30 ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬት ጉዳት ደርሶበታል።
በደረሰው አደጋም 480 አባውራዎች እና 2 ሺሕ 400 የቤተሰብ አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ወደተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች መግባታቸውን የወረዳው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታውቋ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጠለምት ወረዳ ከ100 በላይ አባዎራዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተገለጸ
