ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጡ ወደ 400 የሚጠጉ ተቋማትን የቀዶ ሕክምና ማዋለድ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
"አነስተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የጤና ተቋማትን የቀዶ ሕክምና ማዋለድ አገለግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እናቶች እረጅም ርቀትን እንዳይጓዙ እና እንዳይጉላሉ ያደርጋል" ያሉት የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ ናቸው፡፡
ሚኒስቴሯ አክለውም፤ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ እናቶችን ቁጥር መጨመር፣ ጥራቱ በተጠበቀ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም የወሊድ ተቀማትን በእናቶች አቅራቢያ እንዲኖሩ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሯ የጥር ወርን "ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናትና ለጤናማ እናትነት" በሚል መሪ ቃል፤ እንደሚከበር ትላንት በጥሩ ነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ተናግረዋል።
ይህም የጤናማ እናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38 ጊዜ በሀገራችን ለ19ኛ ጊዜ በጥር ወር እንደሚከበር ነው የተናገሩት፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የእናት ሕይወት ማለፍን በመከላከል ላይ ትኩረት ተሰቶ በተሰሩ ሥራዎች ለውጦች ቢኖሩም አሁንም በቂ አለመሆኑን እና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አክለውም "የጤናማ እናትነት ወር በዚህ ወር ብቻ የሚከበር ሳይሆን፤ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ሥራዎችን አጠናክረን የምንሰራበት ነው" ብለዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ