ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሠው ሀብት ልማት ቢሮ፤ የሠው ሀብት ሥራ አመራር ዘርፍ አመራሮችን ጨምሮ ከ90 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ ሊያከናውን መሆኑን አስታውቋል።
በቢሮው የሰው ሀብት ሥራ አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መላኩ ታምሩ፤ በከተማ አስተዳደሩ ከ90 ሺሕ በላይ የሚሆነው የመንግሥት ሠራተኛ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዛ በላይ የትምህርት ማስረጃ ያለው መሆኑን ከተቋማት ከተውጣጡ የሠው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮች ጋር በተካሄደው ውይይት ላይ ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም በየጊዜው የሚታየውን የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ መበራከትን ለማስቀረት ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ከአመራር እስከ ሠራተኛ ድረስ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሥራው በአፋጣኝ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
የቢሮው የሠው ሀብት ክትትል፣ ድጋፍና ኦዲት ዳ/ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተመስገን በበኩላቸው፤ "የከተማዋን ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ ብሎም የከተማ አስተዳደሩን ተልዕኮ፣ ተግባር እና ኃላፊነት በብቃት ከመፈፀም አንፃር እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ እንግልቶችን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ በየጊዜው ክፍተቶችን ማረም ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
ለዚህም በተቋማት የሚገኙ የሥራ ሂደቶች በትክክለኛ መልኩ የተማረ የሠው ኃይል መያዛቸውን ለማረጋገጥ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን መግለፃቸውን፤ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ