ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ፤ "የምርጥ ዘር አቅርቦትና ተደራሽነት ከማዳበሪያ ስርጭት የተለየ ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

"የአፈር ማዳበሪያ ገንዘብ ካለ መግዛት የሚቻል ሲሆን በአንፃሩ ምርጥ ዘር ግን ለቀጣዩ ዓመት አስቀድሞ መዘጋጀት አለበት" ብለዋል።

ይህን ክፍተት ለመሙላት የሦስት ዓመት የዘር አቅርቦት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የተናገሩ ሲሆን፤ በዚህም የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት 87 በመቶ የሚሸፍኑ አምስት የሰብል አይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የዘር ብዜት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ የእፅዋት ዘር አዋጅ መጽደቁን ገልጸው፤ የዘር አቅርቦት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥቂት አካላት ተሳትፎ ብቻ የሚከወን እንደነበር አስታውሰዋል።

የእፅዋት ዘር አዋጁ አቅም ያላቸው የውጭ ተቋማትን ለመሳብ የሚችል እና የውጭ ቀጥተኛ ሙዓለ ነዋይን ለመሳብ የሚችል እንደሚሆን ገልጸዋል።

አክለውም "አዳዲስ ኩባንያዎች የበቆሎና ሌሎች ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ ጀምረዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ