መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በዛሬው ዕለት ለአምስት አዳዲስ ድርጅቶች የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ለካፒታል ገበያው እንቅስቃሴ ቁልፍ ሚና ለሚኖራቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ፤ ባለስልጣኑ ለአምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።

ይህም ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት መሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ በበኩላቸው፤ ገበያው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም በአግባቡ ሳይሰራበት መቆየቱን አንስተው፤ ይህንኑ ተከትሎ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በማቋቋምና የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
"በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የኢንቨስትመንት ባንኮችንና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ ፍቃድ የተሰጠበት እና አጠቃላይ ፍቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎችን ቁጥር ከአራት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደረገ ነው" ብለዋል፡፡

አዲሶቹ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ስኬትና ዘላቂነት በማረጋገጥ ገበያውን ለመቅረጽ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ፍቃዱ የተሰጣቸው ድርጅቶች ሲቢኢ ካፒታል አ.ማ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ፣ ኢትዮ-ፊደሊቲ ሴኩሪቲስ አ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ፣ ኤች ኤስ ቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስስ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ እንዲሁም፤ ኢኩዥን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ መሆናቸውም ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ