መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ከሁለት ዓመት ደም አፍሳሽ የጦርነት ትግል በኋላ በካርቱም ከተማ የሚገኘውን ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥት መልሶ መቆጣጠሩ ተገልጿል፡፡

በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ከሚመራው የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በሱዳን ጦር በካከል ሲካሄድ በቆየው ጦርነት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋና ከተማዋ ካርቱምን ከነ ቤተ መንግሥቱ ተቆጣጥሮ ሁለት ዓመትን አስቆጥሯል፡፡

Post image

ዛሬ በወጣው መረጃም የሱዳን ጦር በካርቱም የሚገኘውን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ከተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ በማስለቀቅ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ወታደራዊ መሪዉ ናቢለ አብደላህ ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከረጅም ትግል በኋላ የተገኝ ድል በማለት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስኬቱ የተደሰቱ ወታደሮች ሽጉጣቸውን ሲያውለበልቡ፣ ሲጮሁ እና ተንበርክከው ሲፀልዩ የሚያሳይ ፎቶ መታየቱን በቢቢሲ ተረጋገጠ በተባለ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ታይቷል፡፡

Post image

ሠራዊቱ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አር ኤስ ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው የትጥቅ ተቀናቃኝ ከቤተ-መንግሥቱ ከወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ ዋና ከተማዋ ካርቱምን ሙሉ ለሙሉ መልሶ ለመቆጣጠር ተዘጋጅቷል ቢባልም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከቡድኑ እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡

የቡድኑ ካርቱምን ማስመለስ ለሱዳን ጦር ኃይሎች ትልቅ ድል ነው የተባለ ሲሆን፤ ሠራዊቱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በማዕከላዊ ሱዳን አንዳንድ አካባቢዎችም መጠነ ሰፊ ድል ማስመዝገቡም ተመላክቷል፡፡

በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎ መካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት፤ ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ከ14 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡

ይህም ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁን የሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሁለቱ አካላት መካከል በተካሄደ ጦርነት ምክንያ በስፋት የሰብዓዊ መብት ረገጣ መከሰቱን አስታውቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ