መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም፤ አርሶ አደሮች በአጭር ወራት የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ምርታማነታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል።

ሚኒስቴሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮች ክረምትን ጨምሮ በሦስት የምርት ወቅቶች ላይ የተሸለ ምርት እንዲያመርቱ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የሚንስትሩ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ከበደ ላቀው ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ለበጋ መስኖ እና ለበልግ አምራች ገበሬዎች የቴክኖሎጂ እና የግብዓት አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከአቅርቦት ተደራሽነት በተጨማሪም የሥልጠና፣ የውይይት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ግብርናውን ማዘመን ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወትም ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ፤ ከዛሬ ጀምሮ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑት ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙ አስታውቋል።

ይህም ሁኔታ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰትን ስለሚጨምር ወደ ተለያዩ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ የሚገባውን የውኃ መጠን ከመጨመር አንጻር አዎንታዊ ጎን እንደሚኖረው ገልጿል።

በአንጻሩ ግን ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችልም ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።

ስለሆነም የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የጎርፍ ፍሳሽ ማፈሰሻ ቦዮችን በማፅዳት ሊከሰት የሚችልውን ተጽዕኖ ለመከላከል ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ