መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ መፈጸም እጅ ከፈንጅ የተያዙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ቢወሰድም፤ አሁንም ወረራውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ተግዳሮት እየተፈጠረበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
አሐዱም "በ2017 ሰባት ወራት ውስጥ፤ ከሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ግለሰቦችስ ምን ሕጋዊ እርምጃ ተወሰደባቸው?" ሲል ባለስልጣኑን ጠይቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት የምስራች ግርማ በሰጡት ምላሽ፤ በተያዘው ስድስት እና ሰባት ወራት ውስጥ ወደ መሬት ባንክ የገባን መሬትን በግልፅ ለመውረር የሞከሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሕገ-ወጥ ወንጀል የተሳተፉ ምን ያህል እንደሆኑ ይፋዊ ቁጥር ከመናገር የተቆጠቡት ዳይሬክተሩ፤ "ነገር ግን ባለስልጣኑ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ ችሏል" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
"እንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ወረራ ለመፈጸም ከተሞከሩባቸው ከፍለ ከተማዎች መካካል፤ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው" ሲሉም የኮሜኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን የደንብ ቁጥጥሩን ሙሉ ለሙሉ በብቸኝነት ለመቆጣጠር ተግዳሮት ስለሆነ፤ ይህን ችግር ለመቀነስ ከተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአሰራር ስርዓቱን በቀጣይ ለማዘን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በአንድም በሌላም መልኩ በየትኛውም ክፍለ ከተማ በሕገ-ወጥ ሥራ ላይ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ለመቆጣጣጠር በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 167/2016 ዓ.ም ላይ በወጣው ሕግ መሠረት፤ ደንብ ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የሚጣልባቸው ቅጣት ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ እንዲጨምር መደረጉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ