ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የፓርቲዎች ውህደትን በአብላጫ ድምጽ ማድቁን ተከትሎ፤ በርካታ ፓርቲዎች ከህወሓት ውጪ ወደ ውህደቱ የተቀላቀሉ ሲሆን ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመስርቷል። በዚህም በርካታ የፓርቲ አባል እንዳሉት ሲገለጽ ቆይቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በሰጡት መግለጫ፤ የፓርቲው አባላት ቁጥር 15 ነጥብ 7 ሚሊየን መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው ይኼን የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤውን በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል ከአርብ ከጥር 23 - 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአድዋ ድል ሙዚየም ይካሄዳል።
በጉባኤው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የኢንስፔክሽን እና ስነምግባር ኮሚሽን እንዲሁም የጉባኤ ተሳታፊዎች በአጠቃላይ 1 ሺሕ 700 የሚሆኑ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና 15 የሚሆኑ የውጭ ሀገራት እህት ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ አንስተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በጉባኤ በመጀመሪያው ጉባኤ የተቀመጡ ጉዳዮች ተፈጻሚነታቸው እንዲሁም መሻሻል የሚፈልጉት ስራዎች ማሻሻል ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።
እንዲሁም ፓርቲውን ብሎም የመንግሥትን አቅም የሚያጠነክሩ ውሳኔዎችን አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።
"ዘላቂ ሰላምን ብሎም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉ ውሳኔዎችን ይሰጣሉ ሲሉ" የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ