ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሚጥል ሕመምን ለማከም የሚችሉ በቂ የጤና ባለሙያዎች አለመኖር፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሕመሙ ትኩረት እንዳይሰጥ በኢትዮጵያ ኬር ኤፕለፕሲ ማሕበር ለአሐዱ አስታውቋል።
በተጨማሪም በህብረተሰቡም የሚጥል ሕመም እንደሚታከም እንዳያውቅ ማድረጉ የበሽታው መባባስ መንስኤ መሆኑን ማህበሩ ገልጿል።
ለሕመሙ የሚሰጠው የተሳሳተ ግንዛቤ በተለይ የሚጥል ሕመምን ከመንፈስ ጋር በማገናኘት እና ወደ ሕክምና ቦታ አለመውሰድ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን የማሕበሩ ሥራ አስኪያጅ አብይ አስራት ተናግረዋል።
"የሚጥል በሽታ መንስኤዎች እስካሁን በግልጽ የማይታወቅ ሲሆን፤ በብዛት ግን በተፈጥሮ፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በራስ ቅል ላይ በሚደርሱ አደጋዎች እና ኢንፌክሽኖች፣ በስትሮክ እና በሌሎች መሰል ምክንያቶች ሳቢያ ይከሰታል" ብለዋል።
ምን ያህል የሚጥል በሽታ ታማሚዎች እንዳሉ በቂ ጥናቶች አለመኖር፣ የነርቭ ሕመም ሆኖ ሳለ በአእምሮ ሕመም ሥር መደረጉ ሕክምናውን ተደራሽ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አስቀምጠዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም የሚጥል ሕመምን ማከምና መንከባከብ የሚያስችል የጤና ባለሙያ ቁጥርን ለማብዛት እንዲሁም ሕመሙ እንዳይከሰት ለመከላከል በጤና ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በባለድርሻ አካል ትኩረት እንዲሰጥ፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ ጎጂ ልማዳዊ አስተሳሰብ እንዲቀየር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላከተ ሲሆን፤ ከእነዚህም ታማሚዎች ውስጥ ሕክምና የሚያገኙት 5 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኬር ኢፕለፕሲ ኢትዮጵያ ከተቋቋመ 9 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ታማሚዎች እንደማንኛውም ሰው መገለል ሳይደርስባቸው የሚኖሩበት መንገድ ለማመቻቸት አላማው አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ