ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጊዜ ወዲህ 'ታሪካዊ' ሲል የጠራውን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን በ2014 ዓ.ም ማከናወኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ከቀናት በኃላ ደግሞ ከአርብ ጥር 23 እስከ ጥር 25 ቀን 2017 ድረስ ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያድርግ ይጠበቃል፡፡
ፓርቲው ይህንን ጉባኤውን የሚያደርገው በተለይም በሀገር ደረጃ ያጋጠሙት የሰላም እና ጸጥታ ችግሮች እንዲሁም የኑሮ ውድነት ዜጎች እየፈተነ ባለበት ወቅት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አሐዱም "ለመሆኑ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተለይም በኢትዮጵያ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት ውሳኔዎች ሊተላለፉ ይገባል?" ሲል ፖለቲከኞችን ጠይቋል፡፡
"ብልፅግና ፓርቲ በሁለት ጉዳዮች ላዩ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል" የሚሉት ፖለቲከኛ እና የእናት ፓርቲ አባሉ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ "በተለይ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እና የዜጎች የከፋ የኑሮ ውድነትን መቀነስ ላይ ማተኮር አለበት" ብለዋል፡፡
"አሁን በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ችግሮች አሁን ካለበት በዘለለ የከፋ ችግር ሳያመጣ መንግሥት ጠንከር ብሎ ወደ ድርድር መግባት ይገባዋል" ሲሉም ፖለቲከኛው አሳስበዋል፡፡
የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ የዜጎች ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌትነት፤ በዚህ ጉባኤም የፓርቲው ትኩረት በዋናነት መሆን ያለበት ይሄው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌትነት በተለይም በአሁን ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ችግር መፍታት ባለመቻሉ ዜጎች በተለይም ወጣቶች ስደትን ምርጫቸው እያደረጉ መሆኑን በመግለፅ፤ ጉባኤው ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባኤ በዋናነት በሰላምና ደህንነት በተለይም ወደ ድርድር በሚያመጡ መንገደች፣ በኑሮ ውድነት እና ወቅታዊ የትግራይ ፖለቲካዊ ቀውስ ላይ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ብለው እንሚጠብቁ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ከአሐዱ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ራሄል ባፌ ሲሆኑ፤ እሳቸውም "በሀገር ደረጃ ሰላምና ፀጥታን ለማምጣት የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡
"ፓርቲው በዚህ ጉባኤው በዋናነት የሕዝቡን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ያለበት አካልን የሚመራ ፓርቲ በመሆኑ፤ በትክክለኛ እና ሀቀኝነት ሰላምን ለማምጣት መስራት አለበት" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ጉባኤው የብልፅና ፓርቲ የፓርቲውን ጉዳይ የሚመክረበት ቢሆንም ሀገርን የሚመራ መንግሥትን የሚመራ ፓርቲ እንደመሆኑ፤ በተለይም ግጭት ውስጥ ካሉ አካላት ጋር እውነተኛ ስምምነት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አሐዱ ያነጋገራቸው ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤው በተለይም ሕዝብን ሰላምና ደህንነት አንፃር አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለው እንደሚጠበቁ ገልጸዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ፈተና የገጠመው ፓርቲ መሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፤ በተለይም ግጭት፣ ጦርነት እና የኑሮ ውድነት ፈተናዎቹ እንደነበሩ ይገለጻሉ፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ