ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፈው ሳምንት ወደ ዋይት ሀውስ የገቡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ያላቸው ውሳኔዎችን ያስተላለፉ ሲሆን፤ ትላንት ደግሞ መንግሥት የሥርዓተ-ፆታ ለውጥ ለሚያደርጉ ከ19 ዓመት በታች ለሆኑት ወጣቶች ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ እንዲያቋርጥ ወስነዋል፡፡

ትራምፕ ከዚህ በኋላ "የአሜሪካ መንግሥት የፆታ ለውጥን በገንዘብ አያስተዋውቅም፣ አያበረታታም፣ አይደግፍምም" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ ይህን ያስተላለፉትን ውሳኔ የአሜሪካ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ዲፓርትመንት ተፈፃሚ እንዲያደርገው አቅጣጫ መስጠታቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

ይህን ተከትሎም የትራንስጀንደር የመብት ተሟጋች ቡድን፤ "የትራምፕ ንግግር ‘በጣም አስፈሪ ትክክል ያልሆነ፣ ወጥነት የሌለው እና ጽንፍ የያዘ ነው" ሲል ገልጿል።

ይህ የትራምፕ ትዕዛዝ በስርዓተ-ፆታ ለሚሰቃዩ ወጣቶች የተለያዩ ሕክምናዎችን እና ሂደቶችን ይሸፍናል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ባዮሎጂካዊ ጾታቸው ከቀየሩት የጾታ ማንነታቸው ጋር የማይዛመድ ሰዎች የሚሰማቸውን ጭንቀት ለማስውገድ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ‘’ወንድና ሴት የሚባሉ ሁለት ፆታዎች አሉ፤ እነርሱም ሊቀየሩ አይችሉም” ሲሉ በበዓለ ሲመታቸው ቀን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ በሥርዓተ-ፆታ መዛባት ምክንያት ለተለያዩ ጭንቀቶች የተዳረጉ ወጣቶች ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዙ እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ