ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከአዲስ አበባ በተለያዩ መስመሮች የሚወጡ 4 አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡

ጥናቱ እየተደረገ የሚገኘው ከአዲስ አበባ ደሴ፣ ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ እና ከአዲስ አበባ ነቀምት በሚዘልቁት መንገዶች ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡

እነዚህ የፍጥነት መንገዶች የሚገነቡበት የጥራት ደረጃ ፣ የሚኖራቸውም አጠቃላይ የጎን ስፋት ከፍ ያለ እና የሚገነቡበት መልክአ ምድር አብዛኛውን ተራራማ ቦታዎችን የሚሸፍን በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ወጪ እና የቆረጣ ሥራዎችን የሚጠይቁ መሆናቸውን አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

በጥናቱ መሰረት ፕሮጀክቶቹ የሚኖራቸው ርዝመት በአማካይ 300 ኪሜ ሲሆን፤ ግንባታቸውም በተለያዩ ምዕራፎች እና በተወሰነ ኪሎሜትር ተከፋፍሎ እንደሚጀመርም ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶቹ የአዋጭነት እንዲሁም መሰረታዊ የዲዛይንና የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ለዝግጅት ሥራው የሚያስፈልጉ የጥናት ሥራዎችንም ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

አራቱን የፍጥነት መንገዶች ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው በመንግሥትና የግል አጋርነት ትብብር ስለመሆኑም አሐዱ ከአስተዳደሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፍጥነት መንገዶቹ መካከል የአዲስ ጅማ እና አዲስ ደብረ ማርቆስ ፕሮጀክቶች ለገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት የግል አጋርነት ቦርድ የቀረቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹም በቅርቡ ይቀርባሉ ተብለው እንደሚጠበቁ ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ