ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትናንትናው ዕለት በደብረ ብርሀን ከተማ በደረሰ የእሳት እንዲሁም፤ ዛሬ በሐረር ከተማ እና በስልጤ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ በአጠቃላይ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።
በስልጤ ዞን ሁልባራግ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ8 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ አደጋው ዛሬ ከጠዋቱ 3፡30 በወረዳው ሌፎ በሚባል አካባቢ ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ ይጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ከባጃጅ ጋር በመጋጨቱ ደርሷል።
በአደጋው የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል የወረዳው መረጃ ያመላክታል፡፡
የእሳት አደጋው በደብረ ብርሀን ከተማ አየር ሀይል ቀበሌ ትናንት ምሽት 2፡30 የደረሰ ሲሆን፤ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
የከተማው ፖሊስ መምሪያ የትራፊክና መረጃ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር ኪዳኔ በቀለ ለኤፍ ኤም ሲ እንደተናገሩ፤ የእሳት አደጋው የተነሳው ከመኖሪያ ቤት መሆኑንና በቤት ውስጥ ቤንዚን መኖሩ አደጋውን አባብሶ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል፡፡
በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰበት አንድ ግለሰብ በደብረ ብርሀን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምናውን እየተከታተለ መሆኑም ተነግሯል።
በሌላ በኩል በሐረር ከተማ ዛሬ ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ጣሰው ቻለው እንደገለጹት፤ አደጋው የደረሰው በሬ የጫነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪን ለማዳን ሲሞክር በመገልበጡ ነው፡፡
በአደጋውም በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች ሕይወት ወዲያው ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንና በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ ከተጫኑት 15 በሬዎች መካከልም ሦስቱ መሞታቸውንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአይሱዙ አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩን ጠቁመው፤ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ