ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዋሽ ባንክ "ታታሪዎቹ" ሲል በጠራው የሥራ ፈጠራ ውድድር ላሸነፉ ሥራ ፈጣሪዎች ያለማስያዣ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ እያበደረ መሆኑ አስታውቋል።
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ፈጠሪዎችን ውድድር ሲያካሂድ ነበረው ባንኩ፤ በዛሬው ዕለትም ለአንድ ዓመት ሲካሄደው የቆየውን ሁለተኛ ምዕራፍ የሥራ ፈጠራ ውድድር ፍፃሜውን በማድረግ የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል።
የሥራ ማስኬጃ ለማይኖራቸዉ ዜጎች ይህ ውድድር መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን፤ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐዬ ሽፈራው በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ገልጸዋል።
የሥራ ፈጠራዉ ዕውቀት ኖሯቸው በዋስትና ምክንያት የተቸገሩ የሥራ ማስጀመሪያ ላጡ ሥራ ፈጣሪዎች ብድር የማመቻችት ዓላማ ያለው ውድድር መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።
በዛሬዉ ዕለትም በሁለተኛ ምዕራፍ በመጨረሻ ዙር ሲወዳደሩ ከነበሩ 12 ተወዳዳሪዎች መካከል ከአንድ እስከ አምሰት ለወጡ ተወዳዳሪዎች ከ200 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ከ6 እስከ 12 ለወጡ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከ40 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባንኩ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች ያለማስያዣ ብድር መፍቀዱም እንዲሁ ተገልጿል።
"ታታሪዎቹ" በአዋሽ ባንክ የተመዘገበ በየዓመቱ የሚከናወን ውድድር ሲሆን፤ ዓላማውም የሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ መሆኑን አቶ ፀሐዬ ሽፈራው ገልጸዋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ የጀመሪያው የግል ባንክ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከተመሠረተም 30 ዓመታትን አስቆጥሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ