ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ክልል በሚገኙ ቦታዎች በሙሉ የተከሰተ ባለመሆኑ፤ ወደ ቦታው መሄድና መጎብኘት የሚፈልጉ ቱሪስቶች ያለ ስጋት መሄድ እንደሚችሉ የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከተከሰተበት በተለይም ከአዋሽ ፈንታሌ ተራራ ውጪ ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ላይ የተፈጠረ ችግር ባለመኖሩና አሁንም የመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት የሌለበት በመሆኑ፤ ጎብኚዎች እንደቀድሞው ያለ ስጋት መጎብኘት እንደሚችሉ የቢሮው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሀመድ ያዮ ለአሐዱ ገልጸዋል።
"በዚህም መሰረት በክልሉ በቂ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ስላሉና አብዛኞቹ አካባቢዎችም ከመሬት መንቀጥቀጡ የስጋት ቀጠና የራቁ በመሆናቸው፤ ጎብኚዎች መስህቦችን በሚፈልጉት ጊዜ መጎብኘት ይችላሉ" ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለውም በክልሉ በነበረው ጦርነት የቱሪስት ፍሰቱ ቀንሶና ሙሉ በሙሉም ቆሞ እንደነበር አስታውሰው፤ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በክልሉ ያለው ሰላምና ፀጥታ የተረጋጋ በመሆኑ ጥሩ የሚባል የቱሪስት ፍሰት መኖሩን አሳውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ጎብኚዎች መጎብኘት የሚፈልጉትን የአፋር ቦታዎች ለመጎብኘት ሲመጡ ቀጥታ ወደ አፋር ሳያርፉ ሌሎች ክልሎች ላይ እየዋሉና እያደሩ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ቦታዎችን ጎብኝተው ይመለሱ እንደነበረ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በክልሉ ላይ እየዋሉና እያደሩ በርካታ ቀናትንም ቆይተው የሚመለሱ በመሆናቸው፤ ከጎብኚዎች የሚገኘው ገቢ ወደ ክልሉ በቀጥታ በመግባት ማህበረሰቡም ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ