መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለሁለት ሳምንታት ያክል በተለያዩ የአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ መንገዶች ላይ በተደረገ የክትትል እና ድጋፍ ሥራ፤ በተሽከርካሪዎች ላይ በርካታ ጉድለቶች መገኘታቸውን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተለይም ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ የሚደረግላቸው ብቃቱን ሳያረጋግጡ ቦሎ የያዙ ተሽከርካሪዎች በርካቶች መሆናቸውን፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አሰፋ ሀዲስ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የተሸከርካሪ ፍሬን የወለቀባቸው፣ ሰነድ ሳይኖራቸው ቦሎ እንዲይዙ የተደረጉ፣ መብራታቸው የማይሰራ፣ መስታወታቸው የተሰባበረ እና ሌሎችም ክፍቶች በክትትሉ ወቅት መገኘታቸው ተናግረዋል፡፡

አስፈላጊውን እድሳት ሳያደርጉ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ተሽከርካሪዎች ስለመኖራቸውም አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር መንጃ ፈቃድ ሳይዙ የሚያሽከረክሩ፣ በተለይም ቅጣት ላይ እያሉ ተገቢውን የቅጣት ክፍያ በመፈጸም መንጃ ፈቃዳቸውን ሳይወስዱ የሚያሽከረክሩ (በተለይም የታክሲ አሽከርካሪዎች) በብዛት መኖራቸው በክትትሉ መታወቁን ተናግረዋል።

የዚህ ክትትል ዋና አላማ አጠቃላይ ያለውን ሁኔታ ተገንዝቦ ለማስተማርና ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን የገለጹት አማካሪው፤ በክትትሉ በርካታ ችግሮች በታየባቸው አሽከርካሪዎች መስመር ላይ ካሉ አካላት ጋር በጋራ በመተባበር እንደየጥፋታቸው መጠንና አይነት አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አስከፊ የሆነና በዜጎች ላይ አደጋ ሊያደርስ በሚችል መልኩ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ መታሰር የደረሰ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ የትራንስፖርት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ክትትሉ ስለመደረጉም አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ የተደረገው የመንገድ ላይ ክትትል ውጤታማ እንደነበረ የገለጹት አማካሪው፤ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ የሚያሳይና የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የድጋፍ ስርዓቱን በሚገባ ማጤንና በተጠናከረ መንገድ ማስኬድ እንደሚገባ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ክትትሉ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል አቅጣጫ ያስቀመጠም ነበር ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ