የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶቻቸውን፣ የሀገሪቱን የደህንነት አገልግሎት ኃላፊ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከስልጣናቸው አንስተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ከስልጣን መነሳታቸው የተገለጸው በመንግሥት ሚዲያ ላይ በተላላፈ የቀጥታ ስርጭት ላይ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ባለስልጣናቱን ከሥራ ለማባረር የተገደዱበት ምክንያት ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ደቡብ ሱዳን ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2018 ጀምሮ በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡
ይህንንም የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም በ2018 የተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ሀገሪቱ አምስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች አሏት።
በፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ከተነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ውስጥ አንዱ የሆኑት ጄምስ ዋኒ ኢጋ አንጋፋ ፖለቲከኛ እና ጄኔራል ሲሆኑ፤ ከ2013 ጀምሮ በቦታው ላይ የቆዩና የደቡብ ሱዳን ገዢ ፓርቲ የሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ኤስ ፒ ኤል ኤም) ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ።
ሌላው ከስልጣን ምክትል ፕሬዘዳንትና የአገልግሎቶች ክለስተር ዋና ሰብሳቢ እንዲሁም፤ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ህብረት (ኤስኤስኦኤ) አባል የሆኑት ሁሴን አብደልባጊ አኮል ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ለ13 ዓመታት የሀገሪቱ የደህንነት አገልግሎት ኃላፊ ሆነው ያገለገሉትን አኮል ኩር ኩክን በማንሳት በጥቅምት ወር የሾሟቸውንና፤ ለአራት ወራት ያገለገሉትን አኬክ ቶንግ አሌው ከስልጣን አንስተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን እና የደቡብ ምእራብ ምዕራብ ኢኳቶሪያ ግዛት ገዥን ከስልጣን ያነሱ ሲሆን፤ እስከአሁን በባለስልጣናቱ ምትክ አለመሾማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ2018 የሰላም ስምምነት ፕሬዚዳንቱ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የመንግሥት ባለስልጣናትን የመሾም እና የማሰናበት መብት ይሰጣል፡፡
በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው ሀገር ከአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2011 ከሱዳን ተገንጥላ እራሷን በራሷ እያስተዳደረች ነው፡፡
ሀገሪቱ ባሳለፍነው ዓመት ምርጫ ለማድረግ አስባ የነበረ ቢሆንም፤ በሀገሪቱ በተፈጠረ አለመረጋጋት ምክያት ምርጫውን በ2026 ለማድረግ ተገዳለች፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶቻቸውን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነት አነሱ
