ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ካላት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ ለውጭ ሀገራት በሽያጭ ያቀረበቸው አጠቃላይ የኃይል አቅርቦት 500 ሜጋ ዋት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት ሽያጭ ስምምነት ከተፈራረሙት ሀገራት ውስጥ የኬኒያ አንዷ ስትሆን ከኬንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ከዚህ በፊት ከነበሩት እንዲሁም አዲስ ውል ከተፈራረሙት ሀገራት እንደሚለይ ተገልጿል፡፡

ይህም ለውጭ ሀገራት ከቀረበው 500 ሜጋ ዋት ውስጥ 200 ሜጋ ዋት ኃይል በ(ፒክ ሀወር) ወይም የሀይል ተጠቃሚ በሚበዛበት ሰዓት ላይ እንደሚወስዱ ውሉ ማስቀመጡን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

Post image


በዚህም "ገዢው የኃይል ጭማሪ አድርጎ መጠቀም ሻጩ አካልም ኃይል መቀነስ የማይችልበት ውል ነው" ያሉ ሲሆን፤ ውሉን ያላከበረ ተጠያቂ ሊደረግ የሚችልበት አንቀጽ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘም አሐዱ "ተቋሙ ከዚህ በፊት እዳቸውን ያልከፈሉ ሀገራትን ጉዳይ ከምን አድርሶት አዳዲስ ውሎችን ተፈራረመ?" ሲል የጠየቀ ሲሆን፤ ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽም "እዳዋን ካልከፈለችው ሱዳን ጋር ያለው ጉዳይ በድፕሎማሲያዊ መንገድ ይኬድበታል" ብለዋል፡፡

አክለውም "አዳዲሶቹን መክፈል የማይችሉ ሀገራትን በውሉ መሰረት በፍርድ ቤት መጠየቅ ይቻላል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኃይል ሽያጩ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ የተፈራረመችው 500 ሜጋ ዋት ቢሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ ሱዳን የምትጠቀመው የኃይል መጠን ዜሮ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ የተፈረሙ ውሎች ኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ የምታደርግባቸውን ሀገራት ቁጥር ወደ 4 ከፍ አድርጓል መባሉ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ