ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 6 ወራት ከቀረቡት 438 መዝገቦች ውስጥ በ435 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ከ2016 በጀት ዓመት የዞሩ 326 መዛግብቶችን በመያዝ እና በ2017 በጀት ዓመት የተከፈቱ 542 በድምሩ 868 መዛግብቶች የያዙት የገንዘብ መጠን 7 ቢሊየን 320 ሚሊየን 249 ሺሕ 860 ብር ለኮሚሽኑ የቀረቡ ሲሆን፤ ከነዚህ ላይ 438ቱን መዛግብት አከራክሮ በ435 መዝገቦች ላይ ውሳኔውን ማሳረፉን ገልጿል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ከቀረቡለት የታክስ መዝገቦች ውስጥ ከ99 በመቶ በላይ በሚሆኑት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠቱ የገለጸ ሲሆን ይህም ኮሚሽኑ ውሳኔ የመስጠት አቅሙን ማሳደጉን የሚጠቁም ነው ተብሏል ።

የኮሚሽኑ ውሳኔዎች ይግባኝ ተጠይቆባቸው በከፍተኛ ፍ/ቤት ተሽረው ከሚመለሱት መከከል በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በ190 መዝገቦች ላይ በከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ተጠይቆባቸው 8ቱ ብቻ ተሽረው በድጋሚ እንዲመረመሩ መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 5ቱ የፀና አንድ ዕግድ እና ሁለቱ በሒደት ላይ ያሉ ሲሆን፤ ውሳኔዎቹ ጥራታቸውን እና ሙሉ በሙሉ ኮሚሽኑ ነፃና፣ ገለልተኛነት እና ፍትሐዊ የታክስ ሥርዓትን እያረጋገጠ እንዳለ ማሳያ መሆናውን የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በፍትህ ሚኒሰትር በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ የንግድና ሸማቾች እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ችሎቶችን አደራጅቶ በብቃት መምራት መቻሉ ተገልጿል።

ተከራካሪ ወገኖች እኩል የሚደመጡትና በተያዘላቸው ቀጠሮ መሰረት የሚስተናገዱበት እንዲሁም ፍትሐዊ ክርክር የሚደረግበት ነፃና ገለልተኛ ችሎት በኮሚሽኑ በሁለት ፈረቃ እየተሰጠ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ