ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሀሙድ ዛሬ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል።

በአንካራው ስምምነት መሠረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ዲፕሎማሲዊ መሻከር መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዝዳንቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

Post image

"የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ መጡ እላለሁ" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ሁለቱ መሪዎች በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከውይይቱ በኃላ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በመገግለጫቸውም መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም፤ ለቀጣናው መረጋጋት የጋራ መተማመን እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገንቢ ውይይት ማድረጋቸው ተመላክቷል።

Post image

በተጨማሪም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስና ሀገራቱ በየመዲኖቻቸው ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና እንዲኖር ለማድረግ መስማማታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ቀጠናዊ ግንኙነቶችን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና የጋራ እድገትን ለማስቀጠል በትብብር ለመስራት መስማማታቸውም ተነግሯል።

እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ማጠናከር ያለው ጠቀሜታ ላይ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጸጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፤ እያደገ የመጣው የታጣቂ ቡድኖች በቀጣናው ላይ የደቀኑት ስጋት ላይም መነጋገራቸው በጋራ መግለጫቸው ተመላክቷል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በጸጥታ ተቋሟቶቻቸው መመሪያ በመስጠት ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ ለማድረግም መስማማታቸው ተገልጿል።

Post image

በተጨማሪም ሀገራቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት መስመሮችን ለማስፋት እና የጋራ ብልጽግናቸውን ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመላክቷል፡፡

በአንካራ ለተደረሰው የጋራ ስምምነትም በወዳጅነት እና በአጋርነት መንፈስ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ዳግም ያረጋገጡ ሲሆን፤ በስምምነቱ የተቀመጡ የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጋራ መግለጫው አመላክቷል፡፡