መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ማኛውንም አይነት የሃይል እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ይገባል ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ አሳስቧል፡፡
በክልሉ ካለፈው 3 ዓመት ጦርነት በኋላ ግጭቱ በሰላም ስምምነት የተቋጨ ቢሆንም፤ አሁን ደግሞ ህወሓት እርስ በራሱ በገጠመው መከፋፈል ምክንያት የሰላሙ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በአሁን ወቅት በክልሉ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው የገለጸው በክልሉ እየተንቀሳቀሰ ያለው የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ድርጅት፤ "ማንኛውም አካል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለበት" ሲል አስታውቋል፡፡
"የታጠቀ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት፣ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት እንዲሁም ማንገላታት ከማድረስ እንዲቆጠቡ" ሲልም ድርጀቱ ባወጣው መግለጫው አሳስቧል፡፡
የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብሪህ ብርሃኔ፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታጠቁ ሃይሎች በኃይል ወደተለያዩ የክልሉ አስተዳደር ጽ/ቤቶች በመግባታቸው ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች አለመረጋጋት የተፈጠረ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ባሳለፍነው ሳምንት በዓዲ ጉዶም ከተማ በሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እና የሰው ሕይወት መጥፋት ማጋጠሙን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በምስራቃዊ ዞን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ ምስራቅ ዞን ወረዳዎች እንዲሁም በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ሰዎችን በኃይል አፍኖ የማሰርና የማስፈራራት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ መረጃ እንዳላቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ/ም ሌሊት በደቡባዊ ዞን መኾኒ ከተማ አንድ የአካባቢው ሚሊሻ እና አንድ የሠራዊት አባል እንደተገደሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ስለ ሰብዓዊ መብቶች የሚሞጉቱ ተቋማትና ግለሰቦች በትግራይ ክልል ብሎም በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እና ተበዳዮች ፍትህ እንዲያገኙ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሌላ አዲስ የሰብዓዊ ጥሰት መፈፀሙ አስደንጋጭ ጉዳይ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ከ2015 የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ወዲህ በትግራይ ክልል የፖለቲካ ቡድኖች ልዩነታቸው በሰላማዊ መንገድ መፍታት አቅቷቸው የፖለቲካ ውጥረቱ ወደ የኃይል እርምጃ እንዲሄድ ማድረጋቸው፤ የትግራይ ሕዝብ ያገኘው አንፃራዊ ሰላም፣ መረጋጋትና መሠረታዊ መብቶች ወደኃላ የሚመልስ ነው ሲልም ድርጅቱ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እንደ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ሁሉ ከትላንት በስቲያ የኢዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጫው መግለጹ አይዘነጋም፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በትግራይ ክልል የሃይል እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ
