መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከምክር ቤት አባላት በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈፃጸም ላይ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፤ "ስምነቱ ከፍተኛ ድል የተገኘበት ታሪካዊ ስምምነት ነው" ብለዋል፡፡
"ስምምነቱን የተፈራረምነው ያሸፍነውን ጦርነት አቋርጠን ነው፡፡ ይህም ለሰላም ያለንን ከፍተኛ ፍላጎት አሳቷል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"መቀለ ከተማን ለመቆጣጠር አንድ ሁለት ቀን ሲቀረን የሰላም ስምምነት መፈራረማችን ለሰላም ያለንን ፍላጎት ያሳያል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ስምምነቱ በርካታ መሻሻሎች ስለማምጣቱ፣ ጊዜያዊ አስተዳዳር መቋቋሙ፣ የተለያዩ አገልግሎትን የማስጀመር ሁኔታ መኖሩ ከመሻሻሎቹ መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች መካከል የታጣቂዎች ጉዳይ መሆኑንም በምላሻቸው አካተዋል፡፡
የተሃድሶ ሥራውን በተመለከተም "የተሃድሶ ሥራው በተሟላ መንገድ አለመፈጸሙ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ለትግራይ የሚላከው በጀት ለታጣቂዎች ከዋለ ልማት አይመጣም ማለት ነው" ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮች በራያ እና በፀለምት ጥሩ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በወልቃይት አከባቢ የተጀመሩ ሥራዎች ግን በሚገባው መንገድ አልሄዱም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"የፌደራል መንግሥት ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም፤ በተፈናቃዮች ላይ የሚሰራ አፍራሽ ፖለቲካ አስቸጋሪ ሆኖብናል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
"ባለፉት 2 ዓመታት በፕሬዝዳንት ጌታቸው፣ በጄነራል ታደሠ ወረደ እና ጄነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ የተመራው ግዚያዊ አስተዳዳር ጦርነት እንዳይኖር አድርጓል" ብለዋል፡፡
"ምንም እንኳን ቀድሞ በነበረ ጦርነት ላይ ብንወቅሳቸውም ባለፉት ሁለት ዓመት በነበረው ቆይታ ግን ማድነቅ ያስፈልጋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ግዚያዊ አስተዳዳሩ ጊዜው በመጠናቀቁ እሱን በተመለከተ ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል፡፡
በዚህም እስከ ቀጣዩ ምርጫ ያለውን የቆይታ ጊዜ ግዚያዊ አስተዳደሩ የሚመራበትን ሕግ የማሻሻል ሥራዎች እንደሚሰሩና አመራሮች የመቀያየር ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
"የትግራይ ሕዝብ ጦርነት በአይፈልግም፡፡ በውይይታችንም የተረዳነው ይህንን ነው፡፡ ጦርነት የሚፈልጉ ኃይሎች ጦርነት በእንደማያዋጣ መንገንዘብ አለባቸው፡፡ መከላከያ በሌሎች ክልልች ሥራ ላይ ነው በሚል ከሕግ አግባብ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው" ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ