መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ፖለቲካዊ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች መልስ እስካላገኙ ድረስ አሁንም ተጨባጭ የሆነ ድርድር ማድረግ አዳጋች መሆኑን አሐዱ ያነጋገራቸዉ የኢትዮጵያ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ አስታውቀዋል።
መንግሥት ታጣቂ ኃይሎች ከጦርነት ይልቅ የሰላም አማራጭን ሊከተሉ እንደሚገባ እና ድርድር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት ሦስተኛ ወገንን ከመጠበቅ ይልቅ የእርስ በእርስ መተማመንን ለማምጣት ጥሪ ከማድረግ ባሻገር ግንባር ቀደም እርምጃዎችን በመውሰድ አርአያ ሊሆን እንደሚገባ ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።
"በኢትዮጵያ ጠንካራ የንግግር እና የሽምግልና ስርዓት ቢኖርም፤ እየተፈጠሩ ያሉ ፓለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል ደረጃ የዳበረ ባለመሆኑ አሳሪ የሆኑ ማዕቀቦች እና ሕጎችን ፍለጋ ወደ ሦስተኛ ወገን ስናዘነብል ይስተዋላል" የሚሉት የእናት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌትነት ወርቁ ናቸው፡፡
አክለውም "ከሁሉም በፊት መንግስት ፓለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በመመለስ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሊራመድ ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ በበኩላቸው፤ "ሀገራዊ ችግሮቻችንን ለሦስተኛ ወገን ማሳየቱ ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት አንጻር እምብዛም ፋይዳ የለውም" ብለዋል፡፡
"ይሁን እንጂ በራስ አቅም ውስጣዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተከተልነው ያለው የፖለቲካ አካሄድ ስርዓት የመነጋገር እና የመተማመን አካሄድን የተከተለ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ግልጽ እና ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ትግሎችን ለማካሄድ ነጻነትን የሚነፍግ መሆኑን ገልጸዋል።
"ከዚህ ጋር ተያይዞ የ'እንደራደር' ጥያቄዎችን ማቅረብ ብቻውን በቂ አይደለም" የሚሉት ፓርቲዎቹ፤ ውስጣዊ የፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በራስ አቅም ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላትን ወደ ድርድር ለማምጣት እና የውስጥ ሰላምን ለመመለስ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን ልንጠብቅ አይገባም ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ
