ጥር 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሰሜኑ ጦርነትን ተከትሎ ትምህርታቸውን ለመጨረስ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡና የተመረቁ ተማሪዎች፤ የትምህርት ማስረጃ ወረቀታቸውን ማግኘት ባለመቻላቸዉ ለአራት ዓመታት ሥራ ማግኘት እንዳልቻሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በህወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካካል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ፤ 4ተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ለመወጣት መገደዳቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም ተማሪዎቹን የትምህርት ሚኒስቴር በሀዋሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ አድርጓል፡፡
ለአሐዱ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የመካኒካል ምህንድስና ተማሪዎች፤ በተለይም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን በምን ኮርስ እንደሚጨርሱ ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ተነግሯቸውና ተስማምተው ትምህርት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ትምህርታቸውን አጠናቀው ማስረጃቸውን ለመውሰድ ለመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ ግን፤ "ሁለት ክሬዲት ሀወር" መስጠት የነበረው ትምህርት በአንድ በመሰጠቱ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበሩት እነዚህ ተማሪዎች በዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ዲግሪያቸውንም መውሰድ ባለመቻላቸው ለተከታታይ አራት ዓመታት ሥራ መቀጠር እንኳን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
የሌሎች ዲፖርትመንት ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ማግኘት ቢችሉም፤ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተደረጉት የቀድሞ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መካኒካል ምህንድስና ተማሪዎች ግን ማስረጃቸውን እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።
አሐዱም ይህንን የተማሪዎቹን ቅሬታ በመያዝ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴን ጠይቋል።
ዳይሬክተሩም "የተማሪዎችን ጥያቄ በተመለከተ ከመቀሌ ሲሄዱ ያልተካተቱ ኮርሶች የነበሩ በመሆኑና ካሪኩለሙ በመቀየሩ የተፈጠረ ችግር ነው" ብለዋል።
አክለውም "ተማሪዎቹ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲ የሚመጡ ከሆነ እንደ አዲስ መዝግበን ኮርሱን ልንሰጣቸው እንችላለን" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ከትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ ግን የሚመለከተው የጨረሱበትን ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴ ተናግረዋል።
አሐዱም የተማሪዎቹንና የመቀሌ ዩኒቨርስቲን ምላሽ በመያዝ ወደ ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ለጊዜዉ ሊሳካ አልቻለም።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የትምህርት ማስረጃቸው ስላልተሰጣቸው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ
![የትምህርት ማስረጃቸው ስላልተሰጣቸው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2F0a91836591b8119198f943178b953571991c578e-600x600.jpg&w=600&h=600&f=webp)