ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ያለፉትን 6 ወራት ሪፖርቱን በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም 41 ሺሕ 183 የልደት ምዝገባ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በዘገየ እና የግዜ ገደቡ ያለፈበት ወይም እስከ አንድ ዓመት ድረስ ያሉ 195 ሺሕ 402 ሕጻናትን መመዝገብ መቻሉን የገለጸ ሲሆን፤ ለዚህ አፈፃፀም መሻሻል በጤና ተቋማት የተዘርጋው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝ አመላክቷል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ በበጀት ዓመቱ 2ኛ ሩብ ዓመት የእቅዳቸውን 96 በመቶ እንዳሳኩ ተናግረዋል፡፡
የሞት ምዝገባን በተመለከተም 11 ሺሕ 376 ምዝገባ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ ከ2016 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 29 ነጥብ 83 በመቶ የምዝገባ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 15 ሺሕ 574 የጋብቻ ምዝገባ ማደረግ መቻሉን በመግለጽ፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7 በመቶ የምዝገባ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
እንዲሁም በስድስት ወራት ውስጥ 3 ሺሕ 769 ፍቺ ምዝገባ ማደረግ መቻሉን ያስረዱ ሲሆን፤ ይህም ከ2016 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 33 ነጥብ 99 በመቶ የምዝገባ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኃላፊው በዛሬው መግለጫቸው፤ የውጭ ሀገር ጉደፈቻ ከተከለከለ በኃላ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረው፤ ኤጀንሲው ባለፉት 6 ወራት ከተከናወኑ 47 የጉዲፈቻ ጉዳዮች መካከል 24ቱ እንደተመዘገቡ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማዋ በሁለት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ውስጥ 268 ሺሕ 470 የነዋሪነት መታወቂያ መሰጠቱን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ተቋሙ ታግደው የነበሩ አገልግሎቶችን ችግር መፍታቱን የገለጹት አቶ ዮናስ፤ በዚህም 25 ሺሕ 581 የክልል መሸኛዎች ትክክለኛነት እንዲጣራ ለክልሎች መላኩን በመግለጽ፤ አገልግሎት ለማግኘት ሪፖርት ያደረጉ 9 ሺሕ 504 አመልካቾችን መሸኛ መርምሮ የነዋሪነት ምዘገባ አድርገው አገልግሎት እንዲያገኙ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከ41 ሺሕ በላይ የልደት ምዝገባ ማከናወኑን የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ
በስድስት ወራት ውስጥ 3 ሺሕ 769 ፍቺ መመዝገቡ ተገልጿል