ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ወደ ሰዎች የሚተላለፍ ሕመም ያለባቸው እና የሕመም ምልክት የሚያሳዩ እንዲሁም፤ ባለቤት እና ተንከባካቢ የሌላቸውን ውሾች ለማስወገድ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

መድኃኒቶቹ ወደ ሀገር እንዳይገቡና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተደረገው በዓለም ጤና ድርጅት ክልከላ መሆኑን፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብሔራዊ የውሻ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ዶክተር ወንዱ መንገሻ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ወንዱ የክልከላቸውን ምክንያት ሲያስረዱ፤ "መድኃኒቱ ለአካባቢ ብክለት የሚያጋልጡ ቅመሞችን የያዘ በመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተደርጓል" ብለዋል፡፡

በተያያዘም አሐዱ "በተለምዶ 'የእብድ ውሻ በሽታ' በመባል የሚታወቀው እና በበሽታው ከተያዙ ውሾች በንክሻ ወደ ሰው የሚተላለፈው በሽታ የመከላከያ ክትባት ለጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚሰጥበት ምክንያት ምንድነው?" ሲል የውሻ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪውን ጠይቋል፡፡

አስተባባሪው በምላሻቸው፤ "የመከላከያ ክትባቱ የሚሰጠው ለጤና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የክትባቱ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ፤ ሁሉም የጤና ተቋማት መድኃኒቱን ለማስቀመጥ የሚያስችል ማቀዝቀዣ ስለሌላቸው፣ እና በተያያዥ ምክንያቶች ክትባቱ እንደልብ እንዳይገኝ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የስትራቴጂ ክለሳ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር መንገሻ፤ ዋጋው ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ