ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ባለፈው የታሕሳስ ወር በቱርክ አንካራ የተደረሰው ስምምነት፤ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ማሳያ መሆኑን አሐዱ ያነጋገራቸው ምሁራን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት ስለመስማማቷ መግለጿን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀ የከረረ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ አለመግባባቶችን ፈጥሮ ቆይቷል።

በሁለቱን ሀገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በቱርክ አደራዳሪነት በመፍታት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሀሙድ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

አሐዱም የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ፤ በጉዳዩ ላይ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡

"ሁለቱ ሀገራት የደረሱበት ስምምነት ብሎም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ የተከተለችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ አካሄድ ማሳያ ነው፡፡" ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት ዶ/ር ተሻለ ሰብሮ ናቸው፡፡

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው መልስ ወደ ግብፅ ማቅናታቸውን ያሰኑት የቀድሞው ዲፕሎማት፤ "ሀገሪቱ የምታደርገውን እቅስቃሴ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራን ብሎም የደራዳሪነቱን ሚና የተጫወተችው የቱርክን እንቅስቃሴም ቢሆን መከተታል የሚያስፈልግ መሆኑን አንስተዋል።

አክለውም "ሶማሊያና ኢትዮጵያ የደረሱት ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን “ውሃ የሚከልሱ አካላት" ሲለሚኖሩ ግኝኙነቱን የተሻለ አድርጎ ማቆየት ግዴታ ነው" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት ቀድሞ የነበረና ጥሩ የሚባል ነው" ያሉት ደግሞ፤ አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ጥላሁን ሊበን ናቸው።

"አሁን የተደረገው ስምምነት እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጉብኝት የዲፕሎማሲ ግብ የታየበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

አክለውም "የሀገራቱ ግንኙነት በሻከረበት ወቅት ከሁለቱም ሀገራት አላስፈላጊ የሆኑ ንግግሮች ነበሩ" ያሉ ሲሆን፤ "በፓለቲካና ዲፕሎማሲ ቋሚ ጠላት የሚባል ነገር አለመኖሩ ልብ ሊባል ይገባል" ብለዋል።

"እንደ ሀገር ከየትኛውም ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊኖራት ቢችልም ኢትዮጵያ ነገሮችን በትኩረት መመልከት ያሻታል" ሲሉም የቀደመውን ሃሳብ ተጋርተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ዳግም ለማደስ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው መገለጹ ይታወሳል።

በዚህም ሁለቱም ሀገራት በየመዲናዎቻቸው ሙሉ ተወካይ ዲፕሎማት እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር ባልሳድ ኢትዮጵያ በቅርቡ በሶማሊያ አምባሳደሯን ወደ መቃዲሹ እንደምትልክ የገለጹም ሲሆን፤ ሶማሊያም እንዲሁ አዲስ አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ እንደምትልክ ተመላክቷል።