መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ማንኛውም ግለሰብ ከሀገር ለመውጣት ሲያስብ፤ ሕጋዊ መንገድን ብቻ መጠቀም እንደሚገባው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት ተደጋሚ በራራዎችን በማድረግ በሳውዲ እንዲሁም በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገር የማስገባት ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ከሚሰሩ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢፌዴሪ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይገኝበታል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርም ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ማንኛውም አካል ወደ ውጪ ሀገራት ለመሄድ ሲያስብ ሕጋዊ መንገድን ብቻ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተለያዩ ሥራዎች በጋራ እንደሚሰሩ የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፤ "በተለያዩ የማይመች ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎች በርካታ የሥነ-ልቦና ችግር ውስጥ ቆይተው ይመጣሉ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሚመለሱ ዜጎች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ በርካታ ሥራ ለመስራት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
"ይሁን እንጅ ዜጎች አሁንም በተለያየ ምክንያት ለውጥ ሊፈልጉ ይችላሉ ነገር ግን ማንኛውም ዓይነት እንስቃሴዎችን በሕጋዊ መንገድ ማድረግ አለባቸው" ብለዋል፡፡
"ሕገ-ወጥ መንገዶች መምረጣቸው ከራሳቸው አልፎ በቤተሰብና ሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር መታዘብ ይቻላል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተቻለ መጠን ወደ ሕጋዊ መንገድ መመለስ እንደሚያስፈልግ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በተቻለ መጠን ወደ ውጪ የሚደረጉ ስምሪቶች በሕጋዊ መንገድ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እየተረባበረቡ እንደሚገኝም የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ