መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አደረኩት ባለው ድንገተኛ የምርመራ ሥራ፤ የሕጻናት አልሚ ምግቦችን አለአግባብ በእርዳታ መልክ ሲወስዱ የነበሩ 356 የሚሆኑ ሰዎች መገኘታቸውን ገልጿል።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃድጉ ጸሃዬ፤ በተለያየ መልክ ድጋፍ የሚደረግላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከወረዳ ጀምሮ በሚደረገው ምልመላ ላይ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም በተመረጡ ጥርጣሬ በፈጠሩ አካባቢዎች ላይ በተደረገ የምርመራ ሥራ አለአግባባ የሕጻናት አልሚ ምግብ ሲወስዱ የነበሩ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ መቻሉ ተናግረዋል።

Post image

ይህ "የአመለካከት ችግር ነው" ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ የተረጂነት ስሜትን ለማጥፋት በርካት ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ "ከእኔ ሌላው ይብሳል" የሚለውን አመለካከት ከመፍጠር አንጻር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ለመስራት የመገናኛ ብዙሃኑም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም 'የተስማሚነት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ የተመረጡ እገዛ የሚያፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጡ ለሥራ የሚሆኑ እቃዎች ላይ ከተገቢነት ባሻገር በጠየቁት የሥራ ቁሳቁስ መስራት ይችላሉ' የሚለውም ጭምር እየተረጋገጠ መሆኑን አክለዋል።

በአጠቃላይ እገዛ ለሚደረግላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ከታች ከወረዳ ጀምሮ የሚደረጉ ምልመላዎች ላይ ሰፊ የሆነ ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሃድጉ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ