ጥር 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የከተራና ጥምቀት በዓል በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አከባቢዎችና በተለይም በባቱ ከተማ በተለየ መልኩ በደምበል ሀይቅ ላይ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

በክልሉ በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉንና በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ወደ ባቱ ከተማ እየገቡ መሆኑን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር እንዲሁም ከሀይማኖት አባቶች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መምከራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል። "አካባቢዎችን በጥምቀት በዓል ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል" ብለውናል።

"በባቱ ከተማ በሀይቁ ላይ የሚከናወነውን ሐይማኖታዊ ስርአት ጎብኚዎች ያለምንም ችግር እንዲታደሙ ሥራዎች ተሰርተዋል" ሲሉም አብራርተዋል።

Post image

አያይዘውም ከፀጥታ ጋር በተያያዘ በከተማዋ ስጋት አለመኖሩን አንስተዋል። በዓሉ በሰላም እንዲከበር ጥምር የጸጥታ ኃይሉ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰው፤ ነዋሪው ህብረተሰብም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመጨረሻም በዓሉ በሠላም ተከብሮ በሠላም እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በማሳሰብ ለመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዓሉ የሠላም፣ የአብሮነትና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸዉን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ