ጥር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የምግብ ዘይት ምርት ደረጃውን የጠበቅ እንዲሆን እና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላቱን በተመለከተ፤ የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ መጀመሩን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የምግብ ዘይት ደረጃን ሳያሟሉ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ላይ እስከመዘጋት የሚደርስ የቁጥጥር ሥራ መጀመሩን፤ በሚኒስቴሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርምር እና ልማት ማዕከል የምግብ እና መጠጥ ምርምር ማዕከል ተመራማሪ ፍቅሩ አበበ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"በቫይታሚን እጥረት የሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ የጤና እክሎችን ለመቅረፍ ሲባል 'አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ በብዛት አገልግሎት ላይ ይውላል' ተብሎ በሚታመነው የምግብ ዘይት ላይ፤ ቫይታሚን ኤ እና ዲ3 ለሰው ልጅ ጎጂ በማይሆን ሁኔታ በጥናት ተረጋግጦና ተመጥኖ የተቀመጠውን መጠን ያክል ይጨመራል" ሲሉም ተናግረዋል።

በምርት ሂደቱ ላይ እነዚህ ቫይታሚኖች በበቂ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ታሳቢ ተደርጎ እንደሚጨመርና፤ ኢንዱስትሪዎች የወጣውን ደረጃ የመፈፀም ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልል ጤና እና ንግድ ቢሮዎች የሚመረቱ የምግብ ዘይቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማሟላታቸውን እንደሚቆጣጠሩም አብራርተዋል።

ይህ ምርቶችን በቫይታሚንና ሚኒራል የበለፁ እንዲሆን የሚያስገድደው ደረጃ በምግብ ዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎች ምርቶች ላይም ተግባራዊ የሚደረግ እና የቁጥጥር ሥራው የሚቀጥል መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ