ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የሚገኙ የዓዲ ኢሮብ ወጣቶች እየታፈሱ ወደ ኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እየወሰዳቸው ይገኛል ሲል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አስታውቋል።
አንዳንድ የትግራይ ወረዳዎች በኤርትራ ጦር ከነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ የተያዙ መሆናቸውን በመግለጽ፤ "በተለይም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የዓዲ ኢሮብ ሕዝብ ከፍተኛ በደል እያስተናገደ ይገኛል" ብሏል።
"ነገር ግን የኢፌዴሪ መንግሥት የራሱ ሕዝብ መሆኑን ረስቶ ምንም መፍትሔ ሲሰጥ አይታይም" ሲልም ፓርቲው ገልጿል።
የኢሕአፓ ትግራይ ፅ/ቤት በመግለጫው ወራሪው 'የሻዕቢያ ጦር' ሲል የጠራው አካል፤ የዓዲ ኢሮብ ወጣቶችን እያፈሰ ወደ ሳዋ ወታደራዊ ማሠልጠኛ እየወሰዳቸው መሆኑንና የትምህርት ስርዓቱንም በመቀየር በኤርትራ ትምህርት ስርዓት እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጿል።
በመሆኑም ይህ ከፍተኛ የሀገር የሉአላዊነት ወረራ እንዲቆም በማድረግ የኢሮብ ሕዝብ ነፃ ወጥቶ ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲቀላቀል ማድረግ የኢፌዴሪ መንግሥት ኃላፊነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ