ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በፓርቲው አባላት ላይ እስራት እና ወከባ እየደረሰ መሆኑን በመግለጽ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ76 በላይ አባላቶቹ "ያለፍትሕ" ታስረው እንደሚገኙ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንደሚተገበር እና ይህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ስርዓት ስለመኖሩ በገዢው ፓርቲ በተደጋጋሚ ቢገለፅም፤ ይህ ግን ተግባራዊ ስላለመሆኑ ፓርቲው በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንቅፋት የሆኑ ተግባራት በተለያዩ ጊዜያት ሲፈፀሙ መቆየታቸውንም ገልጿል።
"አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ሊያደርገው የሚችለውን በሰው ኃይል እና ፋይናንስ መደራጀት ለማዳከም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አባሎቻችንን በእስርእና ወከባ ላይ ይገኛሉ" ያለው ፓርቲው፤ ይህ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠውን የመደራጀት መብትን የሚጥስ ስለመሆኑ ገልጿል።
በዚህም "በሀረሪ፣ በደቡብ እና በአማራ ክልሎች በአጠቃላይ ከ76 በላይ አባሎቻችችን ፍትሕ እና ፍርድ ሳያገኙ በእስር ላይ ይገኛሉ" ብሏል።
ፓርቲው አክሎም፤ "ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው በአባሎቻችን ላይ የሚደርሰው እስር፣ ወከባና ግፍ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ላይ አደጋ መደቀን እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኛ አለመሆን አድረገን የምንወስደው ነው" ሲል ገልጿል።
በመሆኑም "ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች የሚገኙ አባሎቻችን እየደረሰባቸው ካለው ግፍ ወከባና እስር ነፃ እንዲሆኑ በአፅንኦት እንጠይቃለን" ሲል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዐት በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም ሲል ኢዜማ ገለጸ
ፓርቲው ከ76 በላይ አባላቶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታስረው እንደሚገኙና አስታውቋል