ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌዴራል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በወረቀት ይሰራ የነበረውን የሀብት ማስመዝገብ ሥራ ሙሉ በሙሉ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ማድረጉን አስታውቋል።

"የሀብት ማስመዝገብ ሥራው በማህበራዊ ትስስር ገጽ መሆኑ ማንኛውም ሰው ካለበት ቦታ ሆኖ የሀብት ማስመዝገብ እንዲችልና በቀላሉ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና የአሰራር ሂደቱን ለማዘመን ነው" ሲሉ የኮሚሽኑ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ ለአሐዱ ገልጸዋል።

የሀብት ምዘገባ ሙስናን ለመከላከል ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ የመንግሥት አሰራር በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመሰረት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

አክለውም ሀብት ማስመዝገብ የመንግሥት ተቋማት እና የሥራ ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆን የግል ተቋማት እና ግለሰቦችም የሚያከናውኑት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አዲስ አሰራር መሰረት "የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ከመወሰዱ በፊት ቅድመ መከላከል ሥራ በመስራት በሂደት ላይ እያለ ንብረት ከመወሰዱ በፊት ማቋረጥ ተችሏል" ብለዋል፡፡

ለዚህም በ25 ዘርፎች ላይ ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራንን በማካተትና የማስተማሪያ ማዕከል በማዘጋጀት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አንስተው፤ የሰዎች አመለካከት ላይ መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በፌደራል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የህብረተሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ የሚያገለግል በራሱ ወይም በቤተሰቡ ያፈራውን ንብረት የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይም ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በራሱና በቤተሰቡ የሚገኝ ሀብት እና የገቢ ምንጭ ማስመዝገብ ግዴታው ስለመሆኑ ተቀምጧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ