ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰው ልጆች ላይ ከተፈጸሙ አሰቃቂ ግፎች በመማር ዓለም ሰላም እንድትሆን ሁሉም ሀገራት ሃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ሲሉ፤ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አቭርሃም ንጉሴ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ኤምባሲው በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ 80ኛውን ዓለም አቀፍ የእልቂት መታሰቢያ ወይም “ኢንተርናሽናል ሆሎኮስት ሪሜምበራንስ ደይ” መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
አምባሳደሩ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታም መታሰቢያ መርሃ ግብሩ በጀርመን ናዚ አስተዳድር የተገደሉ 6 ሚሊዮን አይሁዶችን ለመዘከር የተካሄደ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ "ይህን መሰሉ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዳይደገም ዓለም ካለፈው ትምህርት ሊወስድ ይገባል" ብለዋል፡፡
"በጀርመን ናዚ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ትምህርት በመውሰድ የማንኛውም ሰው ደህንነትና ነጻነት ሊጠበቅ ይገባል" ያሉት አምባሳደሩ፤ "ሆኖም ዓለም ካለፈው አልተማረም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"በዚህም አሁን ላይ በመላው አውሮፓ ፀረ- ሴማዊነት እየተስፋፋ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"በጀርመን የተካሄደውን አይነት ጭፍጨፋ የሚመጣው ለረዥም ጊዜ በሚሰራጭ ጥላቻ ነው" ያሉት አምባሳደሩ፤ መሰል ክስተቶች እንዳይደገሙ ሁሉም ሀገራት ሃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም ከ80 ዓመታት በፊት በአይሁዶች ላይ በናዚ አስተዳድር የተደረገው ጭፍጨፋ በመንግሥታቱ ድርጅት እውቅና ተሠጥቶት በየዓመቱ እንደሚዘከር የተናገሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ሀገራቸው በሃማስ የተፈጸማባትን መሰል ጥቃት እየመከተች ትገኛለች ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ