ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም የፓስፖርት ቀጠሮ ያለፈባቸው ተገልጋዮች በቅጣት የሚስተናገዱበት አሰራር መቋረጡን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
"አዲሱ አሰራር ከታሕሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል" ያሉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፤ 25 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች የቀጠሮ ቀን እንደሚያሳልፉና እነርሱን ለማስተናገድም የተቋሙ ሠራተኞች ከመደበኛው የሥራ ሰዓት በተጨማሪ ትርፍ ሰዓት ለመስራት እንደሚገደዱ አንስተዋል።
በመደበኛው የሥራ ሰዓት ብቻ የማይስተናገደውን ከፍተኛ መጠን ያለው ተገልጋይ እስከ ምሽት 12 ሰዓት እና በእረፍት ቀናት ለሚያገለግሉ የተቋሙ ሠራተኞች፤ ለትርፍ ሰዓት አገልግሎታቸው የሚያገኙት ክፍያ 50 ብር ብቻ መሆኑ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2015/2016 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ላይ በተወያየበት ወቅት ያልተገኙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ጉዳዩን አስመልክተው ከወራት በኋላ በሰጡት ምላሽ "ቀጠሮ ባሳለፉ ተገልጋዮች ላይ የተጣለው የቅጣት አሰራር በፓርላማው ውሳኔ መሰረት ከታሕሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቆም ተደርጓል" ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ35ኛ ዓመት መደበኛ ስብሰባው የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ