ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃ በሚመለከት በሕግ ኃላፊነት የተሰጠዉ የመንግሥት ተቋም አለመኖሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የገለጸ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ገደማ ጥረት ያደረገ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ረቂቅ አዋጅ ጉዳይ እልባት ማግኝት አለመቻሉን ለአሐዱ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የካምፖላ ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግ የሚችለውን አዋጅ እንዲወጣ የሚለውን ለመተግበር ጥረት የተደረገ ቢሆንም አሁንም ተፈፃሚ ሊሆን አልቻለም ተብሏል።

አዋጁ እልባት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ የምላሽ እና የመከላከል ሥራዎችን የሚሰሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በበላይነት የሚመሩ ተቋማት እና ኃላፊነትን የሚሰንድ አዋጅ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት፤ በኮሚሽኑ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብቶቾ የሥራ ክፍል ኃላፊ እንጉዳይ መስቀሌ ናቸው።

ኃላፊዋ "የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃ በሚመለከት በሕግ በግልፅ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት ተቋም አለመኖሩ፤ ተፈናቃዮች በየጊዜው ለሚያጋጥማቸው ችግር እንደ አንድ ምክንያት ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ለረጅም ዓመታት በረቂቅ የቆየውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ችግር እልባት ለመስጠት ተደጋጋሚ የውትወታ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ኃላፊዋ እንጉዳይ መስቀሌ ገልጸዋል።

"ከመንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ውይይይት ቢደረግም አሁንም 'የትኛው የመንግሥት አካል ነው ኃላፊነት የሚወስደው' የሚለው ግለፅ ባለመሆኑ ክፍተት ፈጥሯል" ብለዋል።

የተፈናቃዮች ጉዳይ የተለያዩ ባላድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የሚመለከተውን ሁሉ በማሳተፍ ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

በሕግ ኃላፊነት የተሰጠዉ ተቋም ባለመኖሩ በተለይም በግጭት አካባቢ ያሉ ዜጎችን በሚመለከት ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ መምጣቱንም ዳይሬክተሯ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ