ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የእድሳት ሥራ ተጠናቆ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቡራኬ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ታቦተ ሕጉ ጥንታዊነቱን ጠብቆ ወደ ታደሰው ካቴድራል በመግባት ላይ ይገኛል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ተገኝተዋል።
ከሁለት ዓመት በላይ በዕድሳት ላይ የቆየው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ መልኩ ዕድሳት እንደተደረገለት ተጠቁሟል።
ከተመሰረተ ከ81 ዓመታት በላይ የቆጠረው የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት፤ ከ125 ሚልየን ብር በላይ በሆነ ወጪ መከናወኑን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡