ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በዛሬው ዕለት በ600 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሩስያ የሚገኙትን የጋዝ መሰረተ ልማቶች እና የኢንዱስትሪ ቦታዎችን በበምታት አቃጥለዋል ሲሉ የሩሲያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በሃይል በበለጸገችው በታታርስታን ግዛት አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን የጋዝ ክምችት ጋን በመምታቱ በካዛን ከተማ አቅራቢያ እሳትና ጢስ መታየቱን የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃኖች የዘገቡ ሲሆን፤ ይህንንም የግዛቱ አስተዳደር አረጋግጧል።
“ከካዛን በስተደቡብ ምዕራብ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በሚገኘው የሳራቶቭ ክልል፣ በኤንግልስ ከተማ ውስጥ ግዙፍ የሆነ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሁለት የኢንዱስትሪ ቦታዎች ላይ ጉዳት አድርሷል” ሲሉም የግዛቱ ገዥ ሮማን ቡሳርጊን ተናግረዋል።
የታታርስታን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሰው አልባ አውሮፕላኑ በካዛን አቅራቢያ በሚገኝ የኬሚካል ፋብሪካ አቅራቢያ የሚገኝ ፈሳሽ ጋዝ ማከማቻ ቦታን በመምታቱ እና የእሳት ነበልባል እና ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ የሚያሳይ ምስሎችን የለጠፉ ሲሆን፤ የአካባቢው መንግሥት በቴሌግራም የመልእክት መላላኪያ ላይ "የድሮን ጥቃቱን ተከትሎ አንድ ጋዝ ታንክ በእሳት ተቃጥሏል" ሲል ተናግሯል፡፡
በጥቃቱ ማንም ሰው አለመጎዳቱንም ባለስልጣኑ አክለው ገልጸዋል።
በጥቃቱ ምክንያት በሳራቶቭ እና ኤንግልስ ያሉ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ማክሰኞ በበይነመረብ ትምህርቶችን እየሰጡ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በአውሮፓውያኑ የካቲት ወር 2022 ሞስኮ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ከላከች በኋላ፤ በግዛቷ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ለመበቀል ዩክሬን ሩሲያ ውስጥ ወታደራዊ እና የኢነርጂ ጣቢያዎችን በየጊዜው በመምታት ላይ ትገኛለች።
አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ዶናልድ ትራምፕ ለሦስት ዓመታት ያህል የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ማሰባቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ግጭቱን ለማስቆም ማንኛውንም ውይይት ከመጀመሩ በፊት፤ ሁለቱም ወገኖች ጠንካራ የድርድር ፍላጎት ማሳየት ይኖርባቸዋል ብለዋል።