ጥር 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ ተሻሽሎ ወደ ትግበራ የገባው የትራፊክ ቅጣት መጠን፤ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ያላገናዘበና ላልተገባ ወጪም የዳረጋቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ለአሐዱ ገልጸዋል።

"ሀገሪቱ ላይ ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በየቦታው ለቅጣት እየተባለ ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ከባድ በመሆኑና ክፍያውም የተጋነነ ስለሆነ በድጋሚ መሻሻል አለበት" ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

"ዝቅተኛ የቅጣት መጠኑ 500 ቢሆንም ቀላል ቅጣት እየተባልን በየሰበቡ ያለአግባብ 1500 ብር እየተቀጣን ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ሕግ ከማስከበር አኳያ የሚሰራው ሥራ ተገቢ ቢሆንም ከቅጣቱ ውድነት በተጨማሪ ሕግ የሚያስከብሩ አካላት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመቅጣት መጠባበቅ እንጂ ምክንያታዊ ሆነው የአሽከርካሪውን ምላሽ መስማት አይፈልጉምና ይህም ሊታረም የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አሽከርካሪዎቹ ለአሐዱ ተናግረዋል።

አሐዱም የአሽከርካሪዎች ቅሬታ ተቀብሎ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣንን አናግሯል።

Post image


የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ በምላሻቸው፤ ሕግና ስርዓትን አክብሮ የሚሰራ አሽከርካሪ የቅጣቱ ሁኔታ ሊያሳስበው እንደማይገባ በመግለጽ፤ "የደንብ መተላለፍ ቅጣት በመጨመሩ ምክንያት ብዙ ጥቅሞችና ለውጦች መጥተዋል" ብለዋል።

"አንዳንድ ጊዜ ግንዛቤ በመፍጠር ብቻ የሚፈለገው ለውጥ አይመጣምና አስተማሪ የሆነ ቅጣት መቅጣት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንዲሆን ያደርጋልም" ሲሉም ገልጸዋል።

ለአብነትም ቅጣቱ ከመሻሻሉ በፊት ምልክቶች በተቀመጡባቸው ቦታዎች ላይ 100 ብር ብቻ ስለነበር የሚያስከፍለው 'ብንያዝም ቀላል ብር ነው የምንቀጣው' የሚል እሳቤ በመፈጠሩ ምልክቶች አላግባብ እየተጣሱ ለአደጋዎች መንስኤ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ስለሆነም እንዲህ አይነቱን ችግር ለማስተካከል ሲባል የትራፊክ ህግን በአግባቡ አለማክበር ቅጣቱ ከፍተኛ መሆኑን መለማመድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"ሆኖም 'በሂደቱ ያለአግባብ ተቀጥተናል' የሚሉ አሽከርካሪዎች ካሉ፤ ደንቡ አሽከርካሪን ብቻ የሚቀጣ ሳይሆን ከሥራ እስከማሰናበት የሚደርስ ቅጣትን በተቆጣጣሪዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል" ብለዋል፡፡

በመሆኑም "በመዲናዋ 11 ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙ ቅርንጫፎች በመሄድ ቅሬታቸውን ማቅረብና ችግሮችን መፍታት ከፍ ካለም ሃያሁለት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በመገኘት ማሳወቅ ይቻላል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ በ2016 ዓ.ም 94 በሚሆኑ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውሰዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ