መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተፈጠሩ ሰዉ ሰራሽ እና ተፈጥሮዊ ችግሮች ምክንያት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ወይም የሰቆጣ ዲክላሬሽን ፕሮግራም በሚፈለገዉ ልክ አመርቂ ውጤት እንዳላመጣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።፡
እ.ኤ.አ. በ2015 በኢትዮጵያ መንግሥት መተግበር የጀመረው ይህ ሀገር አቀፍ ፕሮግራም፤ ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሚደርስባቸውን መቀንጨር በ2030 ለማስቆም ያለመ ነው።
ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ በጦርነት፣ በፓለቲካ አለመረጋጋት፣ በምርታማነት መቀነስ፣ በድርቅ እና በእርዳታዎች መቋረጥ ውጤታማ እንዳልሆነ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ምግብ ዘርፍ ኃላፊ ማስረሻ ተሰማ ገልጸዋል፡፡
ይህም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚመጣውን የሕጻናት መቀንጨርን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
"በሦስት ምዕራፎች የተከፈለውና የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ ያለው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ለውጦች የታዩበት ቢሆንም፤ በውስጣዊ እና ዉጫዊ ችግሮች እየተፈተነ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም "የሰቆጣ ዲክላሬሽን/ የሰቆጣ ቃልኪዳን ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ እየተተገበረ አይደለም" ማለት እንዳልሆነ ኃላፊው አንስተዋል፡፡
የሰቆጣ ዲክላሬሽን በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ላይ የሚከሰትን መቀንጨር ለማስቆም በመንግሥት እና ልማት አጋሮች ትብብር ልዩ ትኩረት በመስጠት ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተሰራበት ስለመሆኑ ኃላፊው አስታውሰዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም በሚፈለገዉ ልክ ውጤት አላመጣም ተባለ
